የንስሃ አገልግሎት
እንኳን ወደ ንስሐ አገልግሎት ገጻችን በደህና መጡ። አገልግሎቱ ምዕመናን ኃጢአታቸውን ለካህን እንዲናዘዙ እና ከአምላካቸው ይቅርታ እንዲቀበሉ ያስችላቸዋል። በተለይ ምዕመናን በቅዱስ ቁርባን ከመሳተፋቸው በፊት መደረግ ስለሚገባው ዝግጅት እና በዘላቂ የክርስትና ህይወት ጉዟቸው የንስሃ አባት ክትትል የሚያገኙበትን መንገድ በትምህርተ ንስሃ እንዲያጸኑ እና ዘለዓለማዊ ሕይወት የሚያገኙበትን መንገድ የሚያሳይ ነው።
የንስሃ ሂደቶች
1
የንስሃ አባት ይያዙ
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን “የንስሐ አባት” ብዙ ጊዜ ካህን ወይም የነፍስ-አባት ተብሎ ይጠራል። ይህ ካህን የንስሐን ኑዛዜ በሚያዳምጥበት፣ መንፈሳዊ መመሪያ ለንስሃ ልጁ በሚሰጥበት እና በቅድስት ሥላሴ ስም የጸሎት ፍጻሜ በሚሰጥበት የንስሐ ቁርባን ውስጥ ጉልህ ሚና ይጫወታል። የንስሐ አባት ከሌልዎት፣ ዛሬውኑ እንዲኖርዎት ቤተ ክርስቲያኒቱ አጥብቃ ትመክራለች እናም የአጥቢያው አባል ወይም ተገልጋይ ምዕመን ከሆኑ የራስዎን የንስሐ አባት ከካቴድራሉ ይያዙ።
2
ሃጢአትን ይናዘዙ
ንስሐ የገቡ ሰዎች ኃጢአታቸውን ለካህኑ ይናዘዛሉ, ስህተታቸውን አምነው እውነተኛ ጸጸታቸውን ይገልጻሉ። "መንግሥተ ሰማያት ቀርባለችና ንስሐ ግቡ" የማቴዎስ ወንጌል ምዕራፍ ፫፥፩
3
ጸሎተ ንስሃ ይቀበሉ
የንስሃ አባትዎ የእግዚአብሔርን ምህረት እና ይቅርታ በመጠየቅ በጸሎተ ንስሃ ይመራል። ይህ ጸሎት ብዙውን ጊዜ በቅዳሴ መካከል ሲጸለይ ሰምተዋል። በጸሎቱ ንስሃ የገቡ/የሚገቡ ሰዎች መንፈስ ቅዱስ እንዲመራቸው እና ሃጢአታቸውን ይቅር እንዲላቸው ካህኑ በተደጋጋሚ ያሳስባል።
4
ኑዛዜ ይቀበሉ
በንስሃ ህይወት ለቀረቡ ሰዎች ካህኑ የኃጢያታቸው ማስተስረያ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም እንደተሰረየላቸው በመግለጽ ይናገራል።
5
ቀኖና ይቀበሉ
ንስሐ የገቡ ሰዎች ከኃጢአት ለመራቅ እና ዳግም ላለመበደል የበለጠ በጽድቅ ሕይወት ለመኖር ያላቸውን ቁርጠኝነት ለማሳየት እንደ ቤተ ክርስቲያኒቱ ስርዓት መሠረት ካህኑ ቀኖና ይሰጣል። ከነዚህም መካከል ጾም፣ ጸሎት ወይም እንደ ምጽዋት ያሉ አንዳንድ የንስሐ ሥራዎችን ንስሃ ለገባው ሰው ካህኑ ሊሰጥ ይችላል።
6
ቡራኬ ይቀበሉ
ንስሃ አባትዎ በንስሃ ህይወት በመመለስዎ የተሰማውን ደስታ ይገልጻል የንስሃ ሂደቱን በቡራኬ ያጠናቅቃል። በቀጣይም በእምነት እና በታማኝነት መንፈሳዊ ጉዞዎን እንዲቀጥሉ ያበረታታል።